ሕዳር 11/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በተለይም በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ሕገ-ወጥ የግመል እርድ መበራከቱን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ገልጿል።

ድርጅቱ ለአሐዱ ሬድዮ እንዳለው፤ ይህ ድርጊት ከወትሮው የተለየና አዲስ ፈተና እየሆነ ይገኛል።

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ ግመሎች ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ታርደው ለሽያጭ እየቀረቡ እንደሆነ ጠቁመዋል። አቶ ሙሉነህ አክለውም፣ "በተለይም ወደ ቦሌ ሚካኤል ባሉ አካባቢዎች የግመል ስጋ በድብቅ አስገብተው የሚሸጡ መኖራቸውን" አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም ሕገ-ወጥ እርድ በሬ፣ ፍየልና በግ በመሳሰሉ እንስሳት ላይ ብቻ ይካሄድ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ግመልም በዚህ ድርጊት ተይዟል ብለዋል።

ሕገ-ወጥ እርድ የሚፈጸመው አስፈላጊው ምርመራ ባልተካሄደበትና ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ሲሆን፤ ስጋውን ማጓጓዝን ጨምሮ መሰል ድርጊቶችን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ደግሞ የሕብረተሰቡን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ፤ ድርጅቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በመነጋገር ለማስተካከል እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

"ሕብረተሰቡ ጥራቱን የጠበቀ ስጋ መውሰድ እንደሚፈልግ እናውቃለን" ሲሉ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ ለዚህም ሲባል ማኅበረሰቡ ሕገ-ወጥ የግመል እርድን ሲመለከት ወዲያውኑ ጥቆማ መስጠት እንደሚገባው አሳስበዋል።

በሌላ በኩል፣ ሕጋዊው የግመል እርድ በቄራዎች ድርጅት ውስጥ በተለይም በአቃቂ ቃሊቲ ቅርንጫፍ በስፋት እንደሚከናወን ተገልጿል።

በሕጋዊ መንገድ ታርዶ የሚቀርበው የግመል ስጋ በስፋት ለሚጠቀሙት የሶማሌና የአፋር ብሔረሰቦች ተደራሽ እንደሚሆንና፤ ስጋውን ለማቅረብ ስምምነት ካደረጉ ልኳንዳ ቤቶች ጋር በጋራ እንደሚሰራበት ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

ግመሎች ወደ ቄራ ገብተው ለመታረድ የሚቆዩበት አግባብ ቢኖር እንኳን፤ ድርጅቱ በራሱ መኖ እያቀረበ በእንክብካቤ እንደሚጠብቃቸው አስታውቀዋል።

የቄራዎች ድርጅት በአማካኝ በቀን ከ7 እስከ 10 የሚደርሱ ግመሎችን እርድ እንደሚያከናውን የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ